የቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ዲያቆናት (clergy)
እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጆችን ከራሱ ጋር ለማስታረቅ የገባው ቃል ኪዳን በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ልዩ፣ ብቸኛና ፍጹም በሆነ ክህነቱ መስዋዕት አቅራቢ ካህን፣ መስዋዕት ተቀባይ አምላክ፣ ራሱም እውነተኛ መስዋዕት በመሆን አዳነን፤ ከበሽታችን ፈወሰን፤ ሞታችንን ሞቶ የትንሣኤ ሕይወትን ሰጠን። በዚህም አጥተነው የነበረው ጸጋችን ተመለሰልን፣ አዲስ ሕይወትም ተሰጠን። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ የፈጸመው የማዳን ሥራ እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ ላሉ ምዕመናን እንዲደርስ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተልን። እነዚህን ምሥጢራት በክርስቶስ ክህነት የሚፈጽሙ አባቶች በአንብሮተ ዕድ፣ በንፍሐተ መንፈስ ቅዱስ ሾመልን። ይህንንም ብሎ እፍ አለባቸው፤ እንዲህም አላቸው ”መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችሁላቸው ይሰረይላቸዋል፤ ይቅር ያላላችኋቸው ግን አይሰረይላቸውም” እንዲል። ዮሐ. ፳፡ ፳፪-፳፫። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን “እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ዐለት ነህ፥ በዚያች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥ የሲኦል በሮችም አይበረታቱባትም። የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ” (ማቴ ፲፮፥፲፰) ብሎ ስልጣነ ክህነትን ሰጠው።
የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን መስዋዕት አድርጎ በማቅረቡ የክህነት አገልግሎት ዋና ይዘት ፍቅር፣ ራስን ለቤተ ክርስቲያን አሳልፎ መስጠት መሆኑን አሳየን። ከጌታችን የባሕርይ ምንጭነት የተገኘው የአዲስ ኪዳን ክህነት ሐዋርያትን አረስርሶና አርክቶ በቂ የሆነ ክህነታዊ ተግባርም አሳይቶ አሁን ባሉ አባቶች ላይ ይገኛል። አምላካቸውን ያገኙ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን የምትፈጽማቸው ምሥጢራት ስላሏት፣ ምሥጢራቱ የሚፈጸሙትም የግድ በካህናት ስለሆነ ክህነት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ አስፈላጊና የማይቀር ነው። ይህም በዓለም ያለው በእግዚአብሔር አርዓያና ምሳሌ የተፈጠረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን እንዲያይበትና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝበት ነው።
ምስካየ ኅዙናን መድሐኔዓለምና ጼዴንያ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን በነሐሴ ወር ፲፱፻፹፮ ዓ. ም. (August 1994) በወቅቱ በነበሩ ጥቂት ምዕመናን ተመሰረተች። ስትመሰረት በአካባቢው ምንም ካህናትና ዲያቆናት ስላልነበሩ ከቶሮንቶና ከሲያትል አባቶች ካህናት አልፎ አልፎ እየመጡ ይቀድሱና ለህዝቡም ቡራኬ ይሰጡ ነበር። እንዲሁም ደግሞ ከኤድምንተንና ከካልጋሪ ወንድሞች እየመጡ ወንጌል ሲያስተምሩ ቆይተዋል። የሌለው እንዳለ እየታሰበ ያለካህን በቴፕ ቅዳሴ እያስቀደሱና እርስ በእርሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ እየተማማሩ ወጣት መዘምራንም በመዝሙር እግዚአብሔርን እያመሰገኑ የቤተክርስቲያኗን ህልውና ይፈታተኑ የነበሩትንም መናፍቃን እየተጋፈጡ የሚያጸና አምላክ አጽንቷቸው ቤተ ክርስቲያኗ ዛሬ ለደረሰችበት ትልቅ ደረጃ እንድትበቃ ታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ አድርገዋል።
በእንደዚህ ሁኔታ የተመሰረተችው የምስካየ ኅዙናን መድሐኔዓለምና ጼዴንያ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ቸርነት በአሁኑ ሰዓት በሙሉ ልዑክ ካህናት አገልግሎት ይሰጥባታል። የተገልጋዮች ምዕመናን ቁጥርም እንዲዚሁ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ አገልግሎቷን እየሰጠች ትገኛለች፡፡
በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት ካህናትና ዲያቆናት በፎቶው ላይ የሚታዩት ናቸው።