የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለምና ጼዴንያ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአጭሩ፡፡
ከ፲፱፻፺፯ ዓ.ም ቀደም ባሉት አመታት በግለሰብ ቤት በጥቂት ሰዎች ዝክርና መታሰቢያዎችን በማድረግ የተጀመረው መርሐ ግብር ከግዜ ወደ ግዜ እየሰፋ በመሄዱ በመጀመሪያ 63st/Fraser በሚገኘው የሰርቢያን ኦረቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመሰባሰብ በካሴት እየተቀደሰ አገልግሎቱ ተጀመረ፡፡ ሲመሰረት ጀምሮ አቡነ ዜና ማርቆስና አባ ወልዴ የዛሬው አቡነ ሉቃስ ከሲያትል ፣
ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ከቶሮንቶ በመመላለስ መንፈሳዊ ትምህርት በመስጠት፣ ምእመኑን በመምከርና በማደራጀት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
የቤተክርሰቲያናችን መስራቾች ቀደም ብለው ከሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ጋር በነበራቸዉ ቅርበት የተነሳ ቤተክረሰቲያኒቱን ህጋዊ ለማድረግ በጠየቁት እርዳታ መሰረት በ1995 (እኤአ) የመጀመሪያዋ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን በቫንኮቨር እንደ ቅርንጫፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በካናዳ በሚል ህጋዊ መጠሪያ ባለዉ የቶሮንቶ ቤተክረሰቲያን ስር ተመሰረተች።
ምንም እንኳን በግዜው ቤተክርስቲያኒቱ ከቶሮንቶ በቅርንጫፍነት ብትመዘገብም የቫንኮቨር ቤተክርስቲያን ሙሉ በሙሉ የአስተዳደር ስልጣን የነበራት በመሆኑ ካህናትንና ዲያቆናትን በማስመጣትና ዛሬ ለረጅም አመታት ያስቆጠረዉን በከተማችን የሚካሄደውን የስፖንሰርሺፕ ፕሮግራም እንዲጀመር በመርዳት ለቤተክረሰቲያናችን ምስረታና እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል። የአባላቱ ቁጥር እያደገ ሲሄድ አገልገሎቱን በልዩ ልዩ ቦታዎች፤ ለምሳሌም በቫንኮቨር፣ በበርናቢና በኒው ዌስት ከተሞች ውስጥ እየተዘዋወረ ሲካሄድ ቆይቷል።
ይህ በእንዲህ እያለ ቆሞስ አባ ወልደ መስቀል ደምሴ ከስዊድን እንዲመጡ ተጠይቆ ከዓመት በላይ መልስ ያልተሰጠበት ፕሮሰስ በመሳካቱ በግንቦት ፲፪ ቀን ፲፱፻፺ (May 1998 GC) የእመቤታችንን ጽላት ይዘውልን መጡ:: በግንቦት ፳፱ ቀን ፲፱፻፺ (June 6 1998 GC) የጰራቅሊጦስ በዓል ዋዜማ ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ኆኅተ ሰማይ ቅድስት ድንግል ማርያም የሚል ስያሜ ሰጥተውን በዓሉ በመስከረም 10 ለጸዴንያ ማርያም ዕለት እንዲከበር አድርገው ፅላቱን በመንበሩ አኖሩልን።
በኋላም በ2001 እ.አ.አ መጨረሻ በዚያን ጊዜ በነበሩ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት ጥረትና በሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ እርዳታ ቆሞስ አባ ገብረኪዳን ከኢትዮጵያ መጡልን:: እሳቸውም ለዓመት ያህል ጊዜ ለብቻቸው ሲቀድሱ ከቆዩ በኋላ በእሳቸው አሳሳቢነትና በሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ተባባሪነት ዲያቆን ኃይለልዑል አካሉ (የዛሬው ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ኃይለልዑል አካሉ) ከኢትዮጵያ መጥተው የቤተክርስቲያኗ አገልግሎት ተጠናከረ:: በመስከረም ፲፱፻፺፭ ዓም (September 2002) የጼዴንያ ማርያም ዓመታዊ በዓል ብፁዕ አቡነ ዜናማርቆስ፤ ብፁዕ አቡነ መልከጸዴቅ፤ ሊቀካህናት ምሳሌ እንግዳ እና ሌሎችም በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ ተከበረ፡፡
የቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት እየሰፋ የአባላቱ ቁጥር እያደገ በመሄዱ በየግዜው የተለያዩ የአስተዳደር ጥያቄዎች ይነሱ ነበር፡፡ በዚህ ምክኒያት በተፈጠረው አለመግባባት ቤተክርስቲያኒቷ ፈተና ውስጥ የገባችበት ሁኔታ ተፈጠረ። ሆኖም ግን ከጊዜ ሂደት እና ከብዙ ለውጦች በኋላ በሊቀካህናት ምሳሌ እንግዳ ስር በመሆን በብሮድ ዌይና ፕሪንስ አልበርት የሚገኘውን የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለቅዳሜ አገልግሎት በመከራየት አገሎግሎቱ እንደ አዲስ ተጀመረ፡፡
ከጊዜ ሀጓላም በብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ መልካም ፈቃድ መልአክ ፀሀይ ቀሲስ አፈወርቅ ብሩ በቋሚነት እንዲያገለገሉን ተደረገ። መልአክ ፀሀይ ቀሲስ አፈወርቅ ብሩ ቤተሰቦቻውን በሲያትል ከተማ ትተው እኛን በማገልገል በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ መልካም ፈቃድ የእመቤታችንንና የልጇን የመደኃኔዓለምን ፅላት በሰኔ 2014 (እ.ኤ.አ) እንድናገኝ አድርገዋል፡፡ በጊዜው ከሲያትል እየመጡ ከሚያጽናኑን መካከል አቡነ ሉቃስ ፤ አቡነ ዮሀንስ ፤ መምህር ገብረህይወት፤ ዲያቆን ክፍሌ፤ ዲያቆን ዳዊትና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቤተክርስቲያናችን ምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓልም እና ፄዴንያ ቅድስት ማርያም በሚለው መጠሪያ ተሰይሞ፣ በጊዜው የነበረው ሰበካ ኮሚቴም መልአከ ብርሀን ቀሲስ ማዕረግንና ዲያቆን አድማሱ ዘበነን በማስመጣቱ እንዱሁም አሁን የምንገኝበትን ሕንፃ ቤተክርስቲያን በመከራየቱ የዘወትር እሁድ የቅዳሴ አገልግሎት በቋሚነት እንዲቀጥል ምክኒያት ሆነ።
በመጨረሻም ሁለቱ ቅዱስ ሲኖዶስ አንድ ከሆኑ በኋላ በምእራብ ካናዳና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ መልካም ፈቃድ የአሁኑ የቤተክርስቲያናችን አስተዳዳሪ መጋቤ ኅሩያን ቀሲስ ኢንጅኔር ፍሬው ዘገየ በ2018 (እ.ኤ.አ) ተመደቡ፡፡ ከዚህም ግዜ ጀምሮ ደብራቸን የወንጌል አገልግሎቷን በማጠናከርና በተለይም አዲሱን ትውልድ በመቅረፅ ዘመኑን በዋጀ የአገልግሎት አውድ ውስጥ ትገኛለች፡፡
በዚህ አጭር የቤተክርስቲያናችን ታረክ ምእመኑ ለሃይማኖቱ ያለውን ፍላጎትና ቅንነት በማሳየት ሁሉም የተቻለውን በማድረግ በአካባቢያችን የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ለመመስረት ይህ ነው የማይባል ተጋድሎና አስተዋፅኦ ላበረከቱት ሁሉ ምስጋናችንን እያቀረብን እኛም የዛሬ ተረካቢዎች የአባቶቻችንን ገድልና ትሩፋት እንድንደግምና የራሳችንን ታሪክ እንድንሰራ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር፤ የድንግል ማርያም አማላጅነት ከሁላችን ጋራ ይሁን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር