የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ (constitution)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስተያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማስፋፋት አገልጋዮቿን መዝግባ ይዛ ሥምሪት እና ምደባ ለመስጠት፣ ችሎታቸውንና ኑሮአቸውን ለማሻሻል፣ ምእመናንን ለማብዛትና በመንፈሳዊ እውቀት ጎልምሰው፣ በምግባርና በሃይማኖት ጸንተው እንዲኖሩ ለማድረግ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ለማሻሻልና በሚያስፈልጋት ማንኛውም ጉዳይ ራሷን ለማስቻል ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ በየደረጃው የሚቋቋም የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ መዋቅርና አሠራር በቃለ ዓዋዲው መሠረት ዘርግታ ትገኛለች፡፡ የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤዎች በሕዝብ በሚመረጡ ካህናት፣ ምእመናን እና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ተሳትፎ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማስፋፋትና አስፈላጊ የሆነውን አቅም ለማጐልበት የሚመክርባቸው፣ የሥራ ክንዋኔዎችና ችግሮች እየቀረቡ የሚገመገሙባቸውና ልምዶች የሚወስዱባቸው፣ ቀጣይ አቅጣጫዎችም እግዚአብሔር ቢፈቅድ በሚል የሚታይባቸው ናቸው። በ1991 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቃለ ዓዋዲ አንቀጽ 61 /2/ /ሀ/ ላይ የሰበካ ጉባኤ የሚኖረውን የምእመናን ድርሻ በተመለከተ፡- ”የሰበካ ምእመናን በገንዘብ አስተዋጽኦ፣ በአስተዳደር፣ በትምህርት፣ በልማትና በማኅበራዊ ኑሮ አገልግሎት በጠቅላላው በሀብት፣ በዕውቀትና በጉልበት በመርዳት በሰበካው ልዩ ልዩ የክፍል ሥራዎች ውስጥ በመሳተፍ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ክርስቲያናዊ ግዴታቸው ነው” በማለት በተደነገገው መሠረት ምእመናን ለቤተ ክርስቲያናቸው የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ሲሰጡ ለሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓላማ መሳካት ትልቅ ድርሻ ያለው ነው፡፡
የምስካየ ኅዙናን መድሐኔዓለምና ጼዴን ያ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ቃለ ዓዋዲውን መሰረት በማድረግና የምንኖርበት ክፍለ ሀገር ህግ (BC Society Act) በሚያዘው መሰረት የተቋቋመች ስለሆነ በየሦስት ዓመቱ በጠቅላላ ጉባዔው በሚመረጡ ከካህናት፣ ከምዕመናንና ከሰ/ት/ቤት በተውጣጡ ሰባት የሰበካ ጉባኤ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ትመራለች። የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤውም ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤው ሲሆን የሚከተሉት የስራ ክፍሎች አሉት፡
፩ኛ) የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት (የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ፣ ም/ሊቀ መንበርና ጸሐፊውን ያቀፈ)
፪ኛ) የማህበራዊ ጉዳዮችና ስፖንሰርሽፕ ማስተባበሪያ ክፍል
፫ኛ) ገንዘብ ቤት
፬ኛ) የንብረትና ሂሳብ ስራዎች ማስተባበሪያ ክፍል
፭ኛ) የሰንበት ት/ቤት ማስተባበሪያ ክፍል
6ኛ) የትምህርት ክፍል
7ኛ) የእቅድና ልማት ክፍል